ዘመነ ኖላዊ

13 days ago
29

ዘመነ ኖላዊ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አከፋፈል መሰረት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በፊት ከታህሳስ 21 እስከ ታህሳስ 28 ቀን ያለው ዘመን
ዘመነ ኖላዊ ይባላል፡፡

ኖላዊ ማለት <<እረኛ>> ወይም <<ጠባቂ>> ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ነቢያት የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው መተንበያቸው እና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑ ቤተክርስቲያናችን እያሰበች የምትዘምርበት፣የምትቀድስበት፣ የምታመሰግንበት ዕለት ነው፡፡

ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል።
በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ የነበረው ሰንበት ይታሰባል። በዚህ ሰንበት ቤተክርስቲያናችን እረኛ የሌለው በግ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ መዝ፦ 79፥1 በማለት ይማፀኑ እንደነበር ታስተምራለች።

ቸር ጠባቂ ጌታችንም የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ <<መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል>> ዮሐ፣ 10፥11 በማለት እውነተኛ እረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ሰጥቷል። ስለራሱም <<መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።>> ዮሐ፦10፥15 በማለት አስተምሯል፡፡
በልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም <<እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል>> መዝ፦22፥1 ተብሎ እንደተጻፈ

በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሀንህንና ጽድቅህን ላክ፣ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን፣ የቀዘቀዘው ፍቅራችንን መልስልን፣
አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ምንም ወደ ማያሳጣን ወደ እውነተኛው እረኛችን ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል።

ለክርስቲያኖች ሁሉ የታመነ ጠባቂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪም <<በጎቼን ጠብቅ>> ብሎ ቅዱስ በጴጥሮስ በኩል አደራ የተሰጣቸው ካህናተ ቤተክርስቲያን የመንጋው ጠባቂ ናቸው፡፡
ነገር ግን በዚህ ሐሰተኛ በበዛበት ዘመን እውነተኞቹን እረኞች ከተኩላዎቹ መለየት ያስፈልጋል፡፡የምንለያቸውም በፍሬያቸው ነው ማቴ፦7፥15
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መልካም እረኛም ለበጎቹ መልካምን ያደርጋል፡፡ተኩላ ግን በጎችን ሊጠብቅ ሳይሆን ሊነጥቅ እንደሚመጣ ሐሰተኞች እረኞችም ምዕመናንን ሊጠብቋቸው ሳይሆን ሊነጥቋቸው ይፍጨረጨራሉ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ልናውቅባቸው ይገባል፡፡

Loading comments...