ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት

6 days ago
24

ዝክረ ቅዱስ ሚካኤል መንፈሳዊ በጎ አድራጎት(መላኩ):
✅ በዓለ ሢመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ
<<ሚካኤል ሥዩም በዲበ ኃይላት፤ በኃይላት ላይ የተሾምክ ሚካኤል>>
ሲል ያመሰገነው ቅዱስ ሚካኤል በኃይላት መላእክት ላይ የተሾመ ሊቀ መላእክት እንደመሆኑ በዓለ ሢመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)
ኃይላት የተባሉት መላእክትም ሰዎች በዓለም ፈተና ውስጥ ሆነው ሰይጣን ሊያደክማቸው ሲፈልግ ኃይልን ብርታትን የሚሰጡ፣ ይህን ዓለም ንቀው በበርሃ ወድቀው ከሥጋ ምኞት ጋር የሚጋደሉትን፣ በከተማም እየኖሩ መንፈሳዊ ትሩፋት የሚያደርጉትን ደግሞ የሚያበረቱ ናቸው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ <<እርሱም ወደ ሰማይ ያረገ እግዚአብሔርም ተቀምጦ ያለ መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም የተገዙለት ነው…>>ሲል <<ኃይላት>> በማለት ያነሣቸው በኢዮር አራተኛይቷ  ከተማ  የሚኖሩትን  ነው፡፡ በእነዚህ ላይ እግዚአብሔር  ቅዱስ ሚካኤልን አለቃቸው አድርጎ ሾሞታል፡፡ ፩ኛጴጥ፦፫፥፳፪
የቅዱስ  ሚካኤል  ሢመት  በነገደ  መላእክት  ላይ ብቻም ግን  አይደለም፤  የእግዚአብሔር  ሕዝብ  በሆኑት  ላይም ጭምር ነው፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ ስንገባ ለቅዱስ ሚካኤል የተሰጠውን ክብርና ባለሟልነት እንዲሁም የሠራቸውን ሥራዎች እንመለከታለን፡፡

✅ በመጀመሪያ ኢያሱ፦5÷13-15 እንዲህ ይላል፡፡
እንዲህም ሆነ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፡፡ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፡፡ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን አለው፡፡ እርሱም አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ፡፡ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድን ነው አለው፡፡ የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን አንተ የቆምህበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን በፊቱ አውልቅ አለው፡፡ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ ይላል፡፡ ይህን ጥቅስ ልብ ብለን ብናጤነው ለሌላው ሁሉ መርህ ይሆናልና ጥቂት ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
እንዲሁም እግዚአብሔር ራሱ ለኢያሱ <<…በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም ከሙሴ ጋር እንደሆነው እንዲሁ ካንተ ጋር እሆናለሁ አልጥልህም አልተውህም፡፡…>>
ኢያሱ፦1÷1-9 በማለት ምን ያህል እንዳከበረው ያስረዳል፡፡ እስራኤላውያን አሞራውያንን በወጉ ጊዜ ቀኑ ስለመሸባቸው ከመደበኛው የተፈጥሮ ሕግ ውጭ ቀኑ እንደማይጨልምና መዓልቱ እንዲረዝም ኢያሱ በጸሎት ፈጣሪውን ስለጠየቀ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ቀኑን አስረዝሞ ከሰማይ በረድ አዝንሞ ጠላቶቻቸውን በማጥፋት የፈጸመውን አስደናቂ ተአምር እንዲህ ብሎ ጸፏል፡፡
<<...ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል (ልመና) የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም>>
ኢያ፦10÷12-14 በማለት ተገልጿል፡፡ በጠቅላላው ከኢያሪኮ ጀምሮ ታላላቅ የአሕዛብ ምሽጐችን አፍርሶ አሕዛብን አጥፍቶ እግዚአብሔር ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ የማለላቸውን የተስፋይቱን ምድር ለልጆቻቸው ያወረሰ ኢያሱ ነው፡፡
ይህ የእስራኤል መሪ በእጅ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ የተገለጸለት ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን አላወቀም፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ከራሱ ወገን ወይም ከጠላቶቹ ወገን የሆነ አንድ ወታደር መስሎት ነበር፡፡ መልአኩ በሰው አምሳል ስለተገለጸለት አላወቀውም ነበር፡፡ ያነጋገረውም ያለ ፍርሃት ያለ ጭንቀት ያለድንጋጤ ወታደሮቹን እንደሚያነጋግር ዘና ብሎ ነው፡፡ ሆኖም ከመልአኩ የተሰጠው መልስ ታላቅ መሪና ነቢይ የሆነውን የኢያሱን አስተሳሰብ ለወጠው፡፡ ይኸውም <<ከወገኖችህ ወይም ከጠላቶችህ አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ>> የሚለውን
ቃል ሲሰማ ኢያሱ በፊቱ የቆመው ተራ ወታደር ሳይሆን የመላእክት ሠራዊት አለቃ ከሙሴ ሳይለይ የእስራኤልን ሕዝብ የሚጠብቅ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን ሲረዳ ለመልአኩ ክብር መስጠት ስለሚገባ የአክብሮት ስግደት ሰገደለት፤ <<ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድነው>> በማለት በትህትና ጠየቀ፡፡ ጌታዬ አንተ ቅዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ለኢያሱ የምትነግረኝ ምንድነው; በማለቱ የእግዚአብሔርን ክብር ለፍጡር መስጠቱ አይደለም መላእክት ጌቶች ይባላሉ፡፡

ከላይ የቀጠለ፦
ጌትነታቸውም የጸጋ ጌትነት ነው፡፡
ኢያሱ መልአኩን ጌታዬ ብሎ ከጠራው እኛማ ኃጢአተኞች ጌታዬ፤ ቀዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ጸልይልኝ መጥተህ አድነኝ…በማለት የአክብሮት (የጸጋ) ስግደት በመስገድ ብንለምነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጭ አልወጣንም፡፡ የፈጣሪን ክብር ለፍጡር አልሰጠንም፡፡ ተሳስታችኋል የሚለን ሰው ቢኖር እኛ አብነት ያደረግነው የእግዚአብሔር ወዳጅ ኢያሱን ስለሆነ ኢያሱም ተሳስተሃል ይባል፡፡ መልአኩም ኢያሱ ያቀረበለትን የአክብሮት ስግደትና ጥያቄ በመቀበል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መልእክት ነገረው፡፡ ኢያሱም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡
የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ለሰው ሁሉ የሚራራና ስለ ሰው ልጆች ሳያቋርጥ ወደ ፈጣሪው የሚለምን ርኀሩኀ ትሑት የሆነው ኃያሉ ቅዱስ ሚካኤል የሠራውን ሥራ የክብሩን ገናንነት ጽፈን ለመጨረስ ስለማይቻለን በዚሁ እናበቃለን፡፡

✅ በዚህ ቀን ይህ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ያወጣበት ነው።
በበረሃ 4ዐ ዓመት የመራቸው፣ ምድር ርስትን ያወረሳቸው መሆኑን ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡
<<…በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፊቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፡፡>> ዘጸ፦14÷15-20
በዚህ መሠረት እስራኤልን ይመራ የነበረው የእዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
ሕዝበ እስራኤልን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻቸው አሕዛብን አጥፍቶ ምድረ ርስትን ምድራዊት ኢየሩሳሌምን እንዳወረሳቸው ዛሬም ይኸው መልአክ ቅዱስ ማካኤል እስራኤል ዘነፍስ የተባልን ህዝበ ክርስቲያንን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻችን ሠራዋተ አጋንንትን እያጠፋ ምድረ ርስት ወደተባለች ሰማየ ሰማያት ያግባን፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ለአዲስ ኪዳን ሕዝብ ምሳሌ ስለሆነ በታሪክነቱ ብቻ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም፡፡

እንዲሁም በኮሬብ ተራራ እግዚአብሔር ለሙሴ ሐመልማል ከነበልባል ተዋሕዶ በተገለጸለት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አልተለየም ነበር፡፡ ዘጸ፦3÷1-6፣ የሐዋ.ሥራ፦7÷30-34
በኦሪት የእግዚአብሔር መልአክ እየተባለ የሚጠራው አብዛኛውን ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ በድርሳነ ሚካኤልም ተጽፎ ይገኛል፡፡ መዝ፦33÷7
<<የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል) እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸዋል በኢሳ፦37÷36 የእግዚአብሔር መልአክ(ቅዱስ ሚካኤል) መጣ፡፡ ከአሞራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ…በማለት ቅዱስ ሚካኤል ሕዝቅያስን እንዴት እንዳዳነው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ሚካኤል ያልረዳው ቅዱስ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
በዳን.10÷13
<<የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ>> በማለት የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ተገልጿል /ዳን.10÷21/፡፡
በዚሁ በትንቢተ ዳንኤል ም.12÷1 ላይ በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል በማለት ታላቅነቱን፤ለሰው ልጆች ሁሉ በአማላጅነቱና በተራዳኢነት የሚቆም እንደሆነ በማያሻማ ቃል ተገልጿል፡፡
ከዚህም ሌላ ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ ከክብሩ ያዋረደው ወደምድር የጣለው ቅዱስ ሚካኤል ቅዱሳን መላእክትን በመምራት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር ስላደረገው ጦርነትና ስለተቀዳጀው ድል ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሀ በማለት ገልጾታል፡፡
<<በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፤ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፡፡ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም፡፡ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው፡፡ ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ ወደ ምድር ተጣለ፡፡ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ…>>
ራእ፦12÷7-9 ዛሬም ቅዱስ ሚካኤል ሰዳዴ አጋንት አጋንንትን የሚያሳድድ በመሆኑ ከሰይጣንና ከሠራዊቱ መከራ እንዲያድናቸው በጸሎት ለሚለምኑት በቃል ኪዳኑ ለሚማፀኑት ሁሉ ፈጥኖ እየደረሰ ይታደጋቸዋል፡፡ በዙሪያቸው እየከተመ አጥር ቅጥር ሆኖ ይጠብቃቸዋል፡፡ከክፉ ነገር ሁሉ ያድናቸዋል።መዝ፦33÷7፡
በመልእክተ ይሁዳ ቁ.9
<<የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም>> በማለት ቅዱስ ሚካአል ዲያበሎስን እንኳ እግዚአብሔር ይፍረድብህ ከማለት በቀር ሌላ ቃል አለመናገሩ ታጋሽነቱን ያሳያል፡፡

የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡

የታላቁ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል
ምልጃውና በረከቱ ከሁላችን ጋር
ይሁን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Loading comments...