መኮሬታ Mekoreta (እልመስጦአግያ)

0 Followers

❖ መኮሬታ፦ ሺዎች ለማዕረገ ነጽሮት በበቁበት በጥንታዊው የሺዎች ቅዱሳን አንድነት ማኅበረ ሥላሴ ገዳም መናኒያን አበው የሚመገቡት ሠርከ ኅብስት #መኮሬታ ይባላል። የሚዘጋጀው ማሽላና ወደሃከር በድንጋይ ወፍጮ (መጅ) ለ2 ለ2 ብቻ ተገርድፎ ተጋግሮ ከሰሊጥ በሚዘጋጅ አፈላሎ (ወጥ) ይበላል። በገዳሙ ብዙ ጊዜ የሚጨለቀው የሱፍና የሰሊጥ ጭልቃ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ለሐምሌ ሥላሴ የማር ብርዝ ይጨለቃል። በቀደሙት ዘመናት ዐምደ ሥላሴ፣ ዘሥላሴ እየተባሉ ተሹመው ማኅበረ ሥላሴ ገዳምን በአበምኔትነት ባስተዳደሩት ቅዱሳን አበው ጊዜ ድርጓቸው #እንኩርኩሪት ሲሆን በቀን አንድ ጊዜ ለቁመተ ሥጋ ብቻ ነበር የሚበላው።። ቅዱሳኑ እህሉን በጥሬው (በወፍጮ ሳይፈጭና ሳይቦካ) በድንጋይ ላይ ብቻ አስጥተው በፀሐይ አብስለው ይመገቡት ነበር። መኮሬታ አዘጋጅተው በገዳሙ እንዲበላ ያደረጉት ከአቡነ ዓምደ ሥላሴ በኋላ ገዳሙን የመሩት ደቀመዝሙራቸው አቡነ ክፍለ ማርያም ሲሆኑ “መጪው ትውልድ እንዴት ይህን ይችለዋል?” ብለው ሱባኤ ያዙ። በሱባዔው መጨረሻም ድንግል ማርያም በብርሃን ተገልጣ ከላይ በገለጽነው መልኩ መኮሬታን አዘጋጅተው እንዲበሉ ገለጠችላቸው።